You are on page 1of 3

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ 2015 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ

መድረክ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ 2015 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ነሐሴ 5/2015 ዓ/ም
ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል ቀርቦ ተገምግሟል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት በዕቅዱ መሠረት የተከናወኑ ተግባራትን
በተገቢው ሁኔታ በመገምገምና በመተቸት በቀጣይ ሊሻሻሉ የሚገቡ ተግባራትን ለይቶ ካለው በጀት ጋር
በማጣጣም በተገቢው ሁኔታ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ያለውን ውስን ሀብት በጥንቃቄ በመጠቀምና የውስጥ
ገቢን በማሳደግ ተቋሙን ወደተሻለ ደረጃ በማሳደግ ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ውጤታማ ሽግግር ለማድረግ
በትኩረት እንዲሠራ የካውንስል አባላት በተዋረድ ላለው የተቋሙ ማኅበረሰብ በተገቢው ሁኔታ ግንዛቤ
በመፍጠር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ዳምጠው አክለውም በ 2015 በጀት ዓመት የትምህርት ጊዜያትን በአግባቡ በመጠቀም የመማር
ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል መቻሉንና እንደ ዩኒቨርሲቲ ከተያዘው ዕቅድ ባሻገር ሀገራዊ የሆኑ የመውጫ እና
የ 12 ኛ ክፍል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተናዎችን በተሳካና ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ማስኬድ
መቻሉን ጠቅሰው ለስኬቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን አካላት አመስግነዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ዕቅድ ዝግጅት ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሰለሞን ይፍሩ
ባቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲውን
ስትራቴጂያዊ መሠረቶች እና መሠረታዊ መረጃዎች፣ የታቀዱ ዋና ዋና ተግባራትና አፈጻጸም፣ የዓመቱ በጀት
አፈጻጸም፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲሁም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን
በማካተት አቅርበዋል፡፡

በመማር ማስተማር ዘርፍ ከተከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል የመምህራን የማዕረግ ዕድገትን አስመልክቶ
የተቀመጠውን መስፈርት ያሟሉ 12 መምህራን የተባባሪ ፕሮፌሰርነት፣ 12 ቱ የረዳት ፕሮፌሰርነት
እንዲሁም ትምህርታቸውን አጠናቀው የተመለሱ 26 መምህራን የረዳት ፕሮፌሰርነት እና 99 ኙ መምህራን
የሌክቸረርነት ማዕረግ ዕድገት ያገኙ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የአገልግሎት ቆይታቸው፣ የትምህርት
ደረጃና የሥራ አፈጻጸም ግምት ውስጥ በማስገባት 18 ቺፍ ቴክኒካል አሲስታንት ማዕረግ እና በሕክምና
ትምህርት (ስፔሻሊስትነት) ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ያጠናቀቁ 12 መምህራን የረዳት
ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለ 2015 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና (Exit
Exam) በተሳካ ሁኔታ መሰጠቱ፣ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሀገር አቀፍ የ 12 ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 37 ሺህ
ለሚጠጉ ተማሪዎች በተሳካ ሁኔታ መሰጠቱና ተማሪዎቹ ወደየመጡበት አካባቢዎች እንዲመለሱ የማስተባበር
ሥራዎች መከናወናቸው፣ ፒጂዲቲ (PGDT)ን ጨምሮ በመደበኛና በኢ-መደበኛ መርሃ ግብሮች በቅድመ
ምረቃና በድኅረ ምረቃ በአጠቃላይ 3,615 ተማሪዎችን እንዲሁም በከፍተኛ ዲፕሎማ 32 መምህራንን
በበጀት ዓመቱ ማስመረቅ መቻሉ ከተከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በማኅ/ጉድኝት ዘርፍ በመካሄድ ላይ ከሚገኙ 782 ችግር ፈቺ ምርምሮች
መካከል 600 አዳዲስ ምርምሮች እና ከ 2014 በጀት ዓመት የተሸጋገሩ 50 ምርምሮች የተጠናቀቁ ሲሆን በሀገር

1
በቀል ዕውቀቶች ዙሪያ 17 ምርምሮች እንዲሁም በማኅበረሰቡ ችግር ላይ ያተኮሩ 12 ግራንድ የምርምር
ፕሮጀክቶች /Grand Research Projects/ ጸድቀው ወደ ሥራ መገባቱ፣ የዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ የውሃ
ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጆርናል /Ethiopian Journal of Water Sciences and Technology/EJWST/
በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሀገር አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱና በዩኒቨርሲቲው የምርምር ትኩረት መስክ ለሚሠሩ
18 የድኅረ ምረቃ የግል ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ መደረጉ በዘርፉ ከተከናወኑ ዐበይት ክንውኖች መካከል
የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተካሄደው በ‹‹ብሩህ ኢትዮጵያ
2015 የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር›› 10 ተማሪዎችን በማሳተፍ ሁለት ተማሪዎች በሀገር ደረጃ ከ 50 ዎቹ
የደረጃ ተወዳዳሪዎች ውስጥ በመግባት እያንዳንዳቸው 260,000 ብር ተሸላሚ መሆናቸውና ዩኒቨርሲቲውም
የዕውቅና ምስክር ወረቀት ማግኘቱ ከተጠቃሽ ጉልህ ተግባራት መካካል ናቸው፡፡

በማኅበረብ ጉድኝት ዘርፍም ለ 5,888 የማኅበረሰብ አባላት የነጻ ሕግ ድጋፍ መደረጉ፣ ለ 50 አካል ጉዳተኞች
የአንድ ዓመት ነጻ የቤተሰብ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ዕድሳት 25,000
ብር ክፍያ መፈጸሙ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ላጡና ለዘማች ቤተሰብ አባላት በድምሩ ለ 115
አባወራዎች 150,000 ሺህ ብር የሚያወጣ 29 ኩንታል የፉርኖ ዱቄት ለማዕድ ማጋራት እንዲውል ለአርባ
ምንጭ ከተማ አስተዳደር መበርከቱ፣ በቦረና ዞን በዝናብ እጥረት ለተጎዱ ወገኖች 35 ኩንታል በቆሎና 35
ኩንታል ሩዝ ድጋፍ መደረጉ፣ በጎፋና ኮንሶ ዞኖች እና በደራሼ ልዩ ወረዳ በዝናብ እጥረት በተከሰተ ድርቅ
ለተጎዱ ወገኖች የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ 2.1 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የምግብ እህል ጥሬ ዕቃ ድጋፍ
መሰጠቱ፣ በሕክምና ላይ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የሚውል 1.5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ
የብርድ ልብስና አንሶላ ድጋፍ መደረጉ፣ የተለያዩ የአካባቢና ደን ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸው፣ የጋሞኛ ቋንቋ
መዝገበ ቃላት የሞባይል መተግበሪያ በማበልጸግ አገልግሎት ላይ እንዲውል መደረጉ፣ 10 የሕግ ግንዛቤ
ማስጨበጫ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ተዘጋጅተው መሰራጨታቸው፣ ምርምርን መነሻ ያደረጉ 31 ችግር ፈቺ
ፕሮጀክት ንደፈ-ሃሳቦች አስፈላጊውን ሁሉ የግምገማ ሂደት አልፈው ወደ ሥራ መግባታቸው፣ በጨንቻ ዙሪያ
የሻማ ቀበሌ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት ላይ መዋሉ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ዐበይት
ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በበጀት ዓመቱ በመደበኛ በጀት 1,412,715,180.00 እና በካፒታል በጀት ብር 898,644,133.96 ለዓመቱ ዕቅድ
ማስፈጸሚያ ተመድቦ መደበኛው በጀት በ 100.37 ፐርሰንት እና ካፒታል በጀት በ 100.23 ፐርሰንት ሥራ ላይ
የዋለ ሲሆን የውስጥ ገቢን ከማሳደግ አንጻርም 67,069,953.07 ብር መሰብሰቡ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ያጋጠሙ ችግሮችንም በተመለከተ በበጀት እጥረት ምክንያት የተለያዩ የታቀዱ የምርምርና የልማት
ተግባራትን በታቀደበት ጊዜና ልክ ለመተግበር አለመቻሉ፣ በምግብ ጥሬ ዕቃና በሌሎች በሁሉም ግብዓቶች ላይ
ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት መኖሩ፣ የሰርቪስ እና የመስክ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ቁጥር ማነስና
አሮጌ መሆን፣ የግንባታ ክንውን መቀዛቀዝ፣ በ 12 ኛ ክፍል የማጠቃለያ ፈተናዎች ምክንያት የመማር
ማስተማር ሂደቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳያልቅ ጫና መፈጠሩ ተጠቅሰዋል፡፡

የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችን በተመለከተ ተሽከርካሪዎችን በማስጠገንና በመከራየት ሥራዎችን


ማከናወን፣ ከገበያ ዋጋ ንረት ጋር ላጋጠሙ ችግሮች የአንዳንድ ሥራዎችን መጠን በመቀነስና የበጀት
ዝውውሮችን አስፈቅዶ መጠቀም መቻሉ ብሎም የግንባታ ተቋራጮች ሥራውን ሙሉ በሙሉ እንዳያቆሙ
የሦስትዮሽ ስብሰባዎችንና ከዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድና ከኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ጋር
ምክክሮችን በማካሄድ፣ የትምህርት ካላንደር ችግር በተመለከተ የትምህርት ጥራት ከማስጠበቅ አኳያ የክረምት
2
ጊዜን በመጠቀም ወይንም ሴሚስተሩን ወደ ሚቀጥለው ትምህርት ዓመት በማሸጋገር መሥራትና መቆየት
ለማይችሉ ተግባራትና ወጪዎች ቅድሚያ በመስጠት በጀትን አስፈቅዶ በማዛወር ሥራዎችን ማስኬድ
ተችሏል፡፡

በግምገማ መድረኩ ከካውንስል አባላት የአፈጻጸም ሪፖርቱን መሠረት ያደረጉ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ
አፈጻጸሞች ዙሪያ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው ኃላፊዎች ምላሽ
ተሰጥቶባቸዋል፡፡

You might also like